የቀብሪደሃር ዩኒቨርሲቲ በ 2014 ዓ/ም የትምህርት ዘመን ከትምህርት ሚኒስቴር የተመደቡለትን ተማሪዎች እንደተቀበለ ይታወቃል፡፡ ይህን ተከትሎ ተቋሙ ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ እና መሰረታዊ በሆኑ የዩኒቨርሲቲዉ ህገ ደንቦች ላይ ገለፃ የማድረግ ፕሮግራም ዛሬ ቀን ግንቦት 27፤ 2014 ዓ.ም የተከናወነ ሲሆን፤ በፕሮግራሙ ላይ ሁሉም የአንደኛ አመት አዲስ ገቢ መደበኛ ተማሪዎች እና በየ ደረጃዉ የሚገኙ የዩኒቨርሲቲዉ አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ በመገኘት በዋናነት ንግግር ያደረጉት የቀብሪደሃር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ኢንጂነር አብዲፈታህ አህመድ ለሁሉም የአንደኛ አመት አዲስ ገቢ መደበኛ ተማሪዎች በሙሉ የሰላም ተምሳሌት ወደ ሆነችዉ ወደ ቀብርደሃር ከተማ እንዲሁም ቀብሪደሃር ዩኒቨርሲቲ በሰላም መጣችሁ!!! እንኳን ደህና መጣችሁ!!! ብለዋል፡፡ በማስከተልም ተማሪዎች ወደ ተቋሙ ሲመጡ ያነገቡትን የመማር እና ጥሩ ዉጤት የመስራት አላማ ላይ ብቻ አተኩረዉ ትምህርታቸዉን እንዲከታተሉ በማስገንዘብ፤ በዩኒቨርሲቲዉ ዉስጥ በሚኖራቸዉ ቆይታ ሁሉ በዩኒቨርሲቲዉ ዉስጥ የሚገኝ ሁሉም አመራር፤መምህር እና የአስተዳደር ሰራተኛ ከጎናቸዉ እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡
በተጨማሪም የቀብሪደሃር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ረዳት ፕሮፌሰር አብዲሰላም አብዲላሂ ባስተላለፉት መልዕክት ዩኒቨርሲቲዉ ተማሪዎችን ለመቀበል በልዩ ሁኔታ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን አስታዉሰዉ በተለይ ከመማር ማስተማር ጋር ተያይዞ ለሁሉም የአንደኛ አመት አዲስ ገቢ መደበኛ ተማሪዎች የሚያስፈልገዉን ሁሉ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁ እና ተማሪዎች ጠንክረዉ በመማር ጥሩ ዉጤት እንዲያስመዘግቡ በመምከር፤ ወደ ቀብሪደሃር ዩኒቨርሲቲ በሰላም መጣችሁ!!! እንኳን ደህና መጣችሁ!!! የሚል መልዕክታቸዉን አስተላልፈዋል፡፡
በማስከተልም አጠቃላይ የአካዳሚክ ጉዳዮች በተመለከተ በቀብሪደሃር ዩኒቨርሲቲ የሬጅስትራርና አልሙናይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት በረዳት ፕሮፌሰር ክበበዉ ባበጌ ገለፃ የተደረገ ሲሆን፤ በማስከተልም በዩኒቨርሲቲዉ ህገ ደንቦች ዙሪያ ዘርዘር ያለ ፕረዘንቴሽን የላይብረሪ እና ዶክመንቴሽን መ/ዳይሬክተር በሆኑት በመ/ር ሙሉሰዉ ቢራራ እና የምርምር እና ማህበረሰብ ም/ፕሬዝደንት ልዩ አማካሪ በሆኑት በመ/ር ቢሻር አህመድ ቀርቦ የአንደኛ አመት አዲስ ገቢ መደበኛ ተማሪዎች ሁሉ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ተደርጓል፡፡ በመጨረሻም ነባር የተማሪ ተወካዮች ከአንደኛ አመት አዲስ ገቢ መደበኛ ተማሪዎች ጋር የመድረክ ላይ ትዉዉቅ በማድረግ፤ የቀብሪደሃር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ኢንጂነር አብዲፈታህ አህመድ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር እና መልካም የትምህርት ጊዜ ምኞት የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡
#uok